ከሊቢያ ዳርቻ ወደ 40 ኪሎሜትር ያህል ርቀጥ ላይ ሆነው አዳኝ መርከብ በመጠባበቅ ላይ ያሉ 104 አፍሪካውያን ስደተኞች። (ሮይተርስ)

ዘገባ፡- አብዱላዚዝ ኦስማንና ኒኮላ ፒኖ
አዘጋጅ፡- ፒተር ኮበስ

ጥር 7/2007 ዓ.ም (በኢት. አቆ.)

መግብያ

አውሮፓ ታይቶ የማይታወቅ ግዝፈት ያለው የፍልሰተኞች መጉረፍ መቀበሏ እንደቀጠለ ባለበት በአሁኑ ወቅት የሦርያን፣ የኢራቅንና የአፍጋኒስታንን ጦርነትየሚሸሹቱ ዜናም፣ ግንባር-ቀደም መሆኑ እየተስተዋለ ነው።

ነገር ግን ከሰሃራ በስተደቡብ ያሉ አፍሪካዊያን ዜና ማለቂያ የሌለው ሥር-ሰደድ አለመረጋጋትና አካባቢያዊ ግጭቶች የሚካሄዱባቸው የኢኮኖሚ ፍልሰተኞች (ድኅነትን የሚሸሹ)ና የስደተኞችዜና የከበደ አደጋና መከራ እስካልደረሰባቸው ድረስ በዓለም ደረጃ የመደመጡ ዕድል እጅግ አነስተኛ ነው፡፡

በ2015 ዓ.ም (እአአ)ብቻ መፍለስ ከጀመሩት 130 ሺህ ገደማ ከሚሆኑት አፍሪካዊያን አብዛኞቹ ሥር ከሰደደውና የዕለት ዕለት አደጋ ከሆነው ከድኅነት እያመለጡ ናቸው።ይህም በአንዳንዶች አባባል – የቅኝ ግዛት ቅሪት ውጤት ነው። ሮም ውስጥ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚኖረው የ16 ዓመቱ ጋምቢያዊ ፍልሰተኛ ሞሮ ሳኔ በግልፅ አስቀምጦታል፤ «የምንፈልገው እንደ ሰው ፍጡር መኖር ብቻ ነው» ሲል።

እጅግ ከራቁ ከሰሃራ በስተደቡብ ካሉ የሳህል አካባቢዎች ሁለት ዋነኛ የስደት ምንጮች እየተነሱ ወደ “ተስፋዪቱምድር” የሚያደርሰውን ጎዳና ሲያያዙ የርስበርስ ትርምስና ጦርነት የበረከተባትን የሊብያን ምድር ማቋረጥ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ሥፍራ ነው የአረብ አብዮትን ተከትሎ በማግሬብ አውራጃ ሁከቱ መንተክተክ ሲጀምር ከመንበራቸው በኃይል የተጣሉት የሊብያው አምባገነን ገዥ ሞአመር ጋዳፊ “ሜዲቴራኒያን የቀውስ (የትርምስ) ባሕር ይሆናል” ያሉት ንግርት ሠመረላቸው፡፡

ከፊታቸው ባሕር ከጀርባቸው ፅንፍ አልባ ውበረሀ።እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ከጉዟቸው ውሣኔ ጋር ፊት ለፊት የሚፋጠጡት! በጠራው በጎ ቀን የሚያማልሉት የደቡብ ጣልያን የባሕር ዳርቻዎች ዘንድ ለመድረስ በማለም (እአአ) በ2015 ዓ.ም ብቻ 3,771 ፍልሰተኞችን የበላው ተገለባባጭና ተለዋዋጭ ማዕበል ውስጥ ጨክኖ መግባት ይኖርባቸው ይሆን?በለስ ቀንቷቸው እዚያ በሕይወት ለደረሱትም እኮ ያች በመንደላቀቂያና መዝናኛ የተሞላች የጣልያን ዳርቻ የገሃነም ደጆች ልትሆንባቸው ጊዜ አይወስድባትም፡፡ እንደመካከለኛው ምሥራቅ መሰሎቻቸው ሁሉ አንዳንዴ አገር-የለሽ የሆኑት ተጓዦች ዕድል አጥፍተውና ክፉውን በደል ሁሉ ፈፅመው በማይጠየቁት ህገ-ወጥ አስተላላፊዎችና ሊቀበሏቸው በማይፈለጉ መንግሥታት ውሣኔ እጅ ላይ ይወድቃሉ፤ ታሪካቸው እንዲህ ነው። 

የኤዲተሩ ማስታወሻ:- ምንም እንኳን “ተፈናቃይ” “ስደተኛ” እና “ጥገኝነት ጠያቂ” በሚሉት አጠራሮች ወይም የቃላት አጠቃቀም መካከል ዓይነተኛ የሚሰኝ ልዩነት ቢኖርም፤ ፈተና፥ ገጠመኝና ልምዶቻቸውን በቃለ ምልልሶቹ ያጋሩትን ግለሰቦች ታሪክ ሙሉ በሙሉ ማግኘት፥ ማወቅና ማረጋገጥ ባለ መቻላችን ግን አጠራሮቹን እንደ አመቺነቱ በመለዋወጥ መጠቀም መምረጣችንን መግለጽ እንወዳለን።

ክፍል አንድ፡ የጉዞ መሥመሮች

ክፍል አንድ፡ የጉዞ መሥመሮች የሚያስገባው መንገድ

አፍሪካውያን ፍልሰተኞች ከኒጄር ወደ ሊቢያ የሚወስደውን አደገኛ ጉዞ ሲጀምሩ። (ሮይተርስ)

ዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት – አይኦኤም ባወጣው መረጃ መሠረት ዘጠና ከመቶ የሚሆኑት የአፍሪካ ፍልሰተኞች ወደ አውሮፓ የሚጓዙት በሊቢያ በኩል አድርገው ነው። አሥር ከመቶው በግብፅ ያሳብራሉ፡፡

ከሴኔጎል፥ ከጋምቢያ፥ ከጋናና ከናይጄሪያ የሚነሱት አብዛኞቹ የምዕራብ አፍሪካ ፍልሰተኞች በሺሆች ኪሎ ሜትሮች የሚለካ ርቀት ሁለት ሣምንታት ያህል ተጉዘው በማሊወይም በኒዠር አድርገው ሳብሃ እምትባለው የሊቢያ ግዛት ይደርሱና ከዚያም ወደ ትሪፖሊ ያቀናሉ። ጉዞው አንዳንዴ ዓመታትም ሊወስድባቸው ይችላል።

አብዛኞቻቸው ኤርትራዊያንና ሶማሊያዊያን የሆኑ የአፍሪካ ቀንድ ፍልሰተኞች የሚጓዙት በኢትዮጵያ፥ በኬንያ፥ በዩጋንዳና በሱዳኖቹ በኩል እያቆራረጡ ነው፡፡

ከግብፅ ተነስተው ሜዲቴራኒያንን ለማቋረጥ በአስተላላፊዎች ጀልባዎች ላይ የነበሩ ፍልሰተኞች በእጅ ሥልኮቻቸው ካነሷቸው ቪድዮዎች የተወሰደ (ምሥሉን ከአንሺዎቹ ፍልሰተኞች ያገኘው የቪኦኤው አብዱልአዚዝ ኦስማን ነው፡፡)

”ሰሃራ በረሃን ማቋረጥ ከባህሩ ላይ ጉዞ አብዝቶ የከበደ ነው። ባህር ላይ ስትሆን ወይ ትሞታለህ ወይ ትተርፋለህ። ለከፋ ስቃይና ማብቂያ ለሌለው ህመም ግን አትዳረግም”

– ሃፍሳ፤ ሶማሊያዊት – ሮም

ሁሉም የጉዞ መሥመሮች የባህር ዳርቻዋ ከጣልያኒቱ ላምፔዱሣ ደሴት ወደ ሦስት መቶ ኪሎ ሜትሮች ወይም 160 ኖቲካል ማይሎች ርቀት ላይ እሚገኘው ሊቢያ ላይ ይገጥማሉ። ላምፔዱሣ ከጣልያን ፔላጂ ደሴቶች ግዙፉ ሲሆን ለአፍሪካ እጅግ ቀርቦ የሚገኘው የአውሮፓ ምድር ነው።

በአውሮፓ ኅብረት መርከብ ላይ የነበሩ ፍልሰተኞች በእጅ ሥልኮቻቸው ካነሷቸው ቪድዮዎች የተወሰደ (ምሥሉን ከአንሺዎቹ ፍልሰተኞች ያገኘው የቪኦኤው አብዱልአዚዝ ኦስማን ነው፡፡)

ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ የአፍሪካ ሃገሮች እየተነሱ በ2015 ዓ.ም (እአአ) ወደ አውሮፓ የጎረፉት ሰዎች ብዛት ከጠቅላላው ፍልሰተኞች ቁጥር 15 ከመቶውን ብቻ ነው የሚይዘው። ይህ አኀዝ የሚያሳየው ግን አህጉሪቱ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ጨርሶ ያላየችውን የስደት ጎርፍ ነው። ሁሉም ፍልሰተኞች [ማለት ይቻላል] ወደ አውሮፓ ሀገሮች የሚበታተኑት በጣልያን በኩል እየገቡ ነው። ኢራቅ፥ ሦሪያና አፍጋኒስታን ውስጥ በሚካሄዱ ጦርነቶች ሳቢያ የተፈናቀሉ ሰዎች በብዛት ገብተው እንዳጨናነቋት እንደ ጎረቤት ግሪክ ባይሆንም፥ ወደ ጣልያን የገቡቱ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ ተተካካይ ነው።

“በዚህ ዓመት ወደ ጣልያን የገባ የተጋነነ የፍልሰተኞች ቁጥር የለም” ብለዋል ዋና ፅ/ቤቱ ሮም የሚገኘው የዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት – አይኦኤም ዳይሬክተር ፍሬደሪኮ ሶዳ፡፡ አኀዙ ባጠቃላይ  ከ2014 ዓ.ም ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም የጎሣና የመጡባቸው አካባቢዎች ስብጥር ግን እንደሚለያይ የአይኦኤም ዳይሬክተር ገልፀዋል፡፡ በዚህ መሠረት ባሁኑ ጊዜ የባልካን ሃገሮችን እያቆራረጡ የሚደርሱት የሦሪያ ፍልሰተኞች ቁጥር ከበፊቱ በብዙ ቀንሷል። አሁን በርክተው የሚታዩት በመሠረቱ የኢኮኖሚ ስደተኞች የሆኑትና በተወሰነ ደረጃ ዐይን ያልተሰጣቸው የምዕራብ አፍሪካ ዜጎች ናቸው። ትኩረት የሚያገኙት ፀጥታ መናጋት ችግርና ሁከት ያሳደዷቸው ካፍሪካ ቀንድ ሀገሮች የሚፈልሱት ናቸው።

ዓለም አቀፍ ፍለሰተኞች ድርጅት ( IOM) የሜዲትሬንየን መዘጋጃ ክፍል ዳይሬክተር ፌዴሪኮ ሶዳ ጋራ የተደረገ ቃለ-መጠይቅ። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

ክፍል ሁለት፡ ሊብያ

ክፍል ሁለት፡ ሊብያ የገደሉ አፋፍ፣ ቁልቁል ወደ ሊብያ መውረድ

በሊቢያ ድንበር አካባቢ በሚገኝ በረሃ ላይ ወድቀው የተገኙ  ነጠላ ጫማዎች። (ሮይተረስ)

ሊብያ ጉዞ ላይ ላሉ ፍልሰተኞች ግራ የምታጋባ ሃገር ናት። ብዙውን ጊዜ የነፍሰ በላው የሰሀራ ምድረ-በዳ ከባድ ጉዞ መዳረሻ ናት። በአነስተኛ ጀልባ ሜዲቴራንያን ባህርን ለማቋረጥ የሚደረግ አደገኛ ጉዞ ዋና መነሻም ናት። ካነጋገርናቸው መንገደኞች ከሞላ ጎደል ሁሉም የጉዟቸው አስከፊና መፃዒ ዕድላቸው የሚወሰንበት ክፍል ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ስርዓት አልበኛነት የሰፈነባት  ሊብያ የወንጀል ቡድኖችና የአሸባሪ ድርጅቶች መጠጊያ ሆናለች። ከሰሃራ በስተደቡብ ያሉ የአፍሪካ ሀገሮች ሰዎች የሥራ ዕድል የሚያገኙባት ማዕከል የነበረችው ሊብያ የዘግናኝ አድራጎቶች መናኸርያ ሆናለች። በቅርቡ የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ሊብያ ውስጥ እዚህም እዚያም ሕግ እናስከብራለን የሚሉ የታጠቁ ቡድኖች፣ ህገወጥ አስተላላፊዎችና በአገር ግዛት ሚኒስቴር ሥር የሚገኙ እጅግ ሰፋፊ እሥር ቤቶችን የሚያስተዳድሩ ባለሥልጣኖች ስለሚፈፅሙት የስቃይና የባርነት አያያዝ፣ ፆታዊ ጥቃትና የዝርፊያ ተግባር በዝርዝር አስፍሯል።

“ሊብያዊያን ድንበር ላይ በጎማ ቧምቧ ይደበድቡናል። አሸዋ ይዟቸው መንቀሳቀስ ያልቻሉትን ተሽከርካሪዎች ገፍተን እንድናወጣ ያስገድዱናል። እፊታችን ሆነው እየበሉና እየጠጡ በሚጠብሰው ፀሃይ አሰልፈው ያቆሙናል።”

– ሑሴን ሙሕዲን፤ ሶማልያዊው በሚላን

ሊብያ ውስጥ ስለሚፈፀሙት በደሎች በሰፊው የተመዘገበ ቢሆንም ብዙ ፍልሰተኞች ስለአደጋው ብዙም እንደማያውቁ የዓለምአቀፍ የፍልሰት ድርጅት ሠራተኛ ሶዳ ተናግረዋል፡- “ህገወጥ አስላላፊዎቹ ጥቃት አድራሾች እየሆኑ መምጣታቸውን አያውቁም” ብለዋል ሶዳ።

ሳማ ቶንካራ የተባለ የ 23 ዓመት ዕድሜ ወጣት “ትሪፖሊ ውስጥ በየቀኑ ስንፏችር ነበር የምንኖረው” ሲል ገልፆታል።

የተሳፈረችበት መርከብ በመገልበጡ ከሜድተሬንያን ባህር የሊቢያ ባህር ሃይል ያዳናት ነይጄሪያዊ ፍልሰተኛ (አሶስየትድ ፕሬስ)

የማሊያ ተሰዳጅ ሳማ ቱንካራ ሊቢያ ውስጥ ስላሳለፈው ጊዜ ሲናገር። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

ክፍል ሦስት፡ እማኝነት

ክፍል ሦስት፡ እማኝነት ማቋረጫውና ምስክሮቹ

ሶማሊያዊ ፍልሰተኛ ራህማ አቡካር አሊና ልጇ ሶፊያ በገልሰንክርከን ሰሜን ራይን- ዌስትፋልያ-ጀርመን። (ቪኦኤ /አብዱላዚዝ ኦስማን)

በጀርመን የባሕር ኃይል መርከብ ሽሌስቪግ-ሆልሽታይን ላይ የተገላገለችው የ33 ዓመት ዕድሜ ያላት የሰባት ልጆች እናት፤ ከሕገወጦቹ አስተላላፊዎች እገታ እንዲለቀቁ ቤተሰቦቻቸው ለያንዳንዳቸው ስምንት ሺህ ዶላር የከፈሉላቸው ሁለት ዕድሜአቸው 16 ዓመት የሆነ ሁለት ኢትዮጵያዊያን፤ በረሃው ውስጥ ሞት በአካባቢያቸው ሲያደባ የራሣቸውን ሽንት ሲጠጡ አይቻለሁ የሚለው የሚለው ሶማሊያዊ፤ እያንዳንዳቸው የየራሣቸው የሆኑ የተለያዩ ታሪኮች አሏቸው፡፡ ድምዳሜዎቻቸው ሁሉ ግን ብዙ አጋጣሚዎችና የእህል-ውኃ ነገር የበዙበትን ሜዲቴራኒያን ባሕርን ያቋረጡበት ሁኔታ ነው የሚወሰኑት፡፡

የቪድዮ እማኝነት፤ ራሕማ አቡካር አሊ፤ ዕድሜ 33፤ ሶማሊያ፡- ራህማ አቡካር አሊ ፍልሰተኞቹን ወደሚያሣፍሩባት ጀልባ የወጣችው ነሐሴ 16 ነበር፡፡ ይህ ጉዞ የአንዳች አዲስ ነገር መጀመሪያ ወይም የሕይወቷ ፍፃሜ ሊሆን እንደሚችል አውቃለች፡፡

ራህማ የእርግዝናዋን የመጀመሪያ አምስት ወራት ያሳለፈችው ከሶማሊያ ተነስታ በሚያንገበግበው ሰሃራ በረሃ ውስጥ ስታቋርጥ ነበር፡፡ ከእግር መንገድ የምታርፈው አንድም ስትተኛ፤ አልያም በጦርነት ከሚታመሱት የምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች በሚሸሹ ሰዎች በሚታጨቁባቸው ዚታዎች ላይ ስትወጣና በጭንቁ ውስጥ ተጨብጣ ስትቀመጥ ነበር፡፡

“የመደንዘዝ ስሜት እየተሰማኝ ነበር፤ በመንገዱ ምክንያት በጣም ደክሞኝ ነበር” – ትላለች ራህማ፡፡ ራህማ ልጇን የትም ብትወልድ አያስጨንቃትም፤ ሊብያ ውስጥ ብቻ አይሁን እንጂ፡፡ ስለዚህም ሊደርስባት የሚችለውን አደጋ ሁሉ እያወቀች እዚያች አንዳች አስተማማኝነት የሌላት የወላለቀች ጀልባ ላይ ወጣች፡፡

“አውሮፓ መድረስ ካልቻልኩ ልጄን እንዳረገዝኩት ለመሞት ዝግጁ ነበርኩ፡፡” – አለች ራህማ፡፡

ይሁን እንጂ ራህማ በጀርመኒቱ መርከብ ላይ ተገላገለችና ከአዲሲቱ ልጇ ከሶፊያ ጋር ድዩሰልዶርፍ ወደሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ሠፈር ጉዞ ጀመሩ፡፡ ራህማ አሁን የጥገኝነት መጠየቂያ ማመልከቻ አስገብታ መልስ እየጠበቀች ነው፡፡

“ሊብያ የሜዲቴራኒያን ሶማሊያ ልትሆን ትችላለች፡፡ ሲሲሊ፣ ክሬት እና ላምፔዱሳ ውስጥ የባሕር ላይ ወንበዴዎችን ወይም ፓይሬቶችን ታያላችሁ፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕገወጥ ፍልሰተኞችን ታያላችሁ፡፡ እዚያው ሽብር ፈጠራም ሲቀጣጠል ታያላችሁ፡፡”

– እነዚህ ቃላት የቀድሞው የሊብያ መሪ የኮሎኔል ሞአማር ጋዳፊ አልጋ ወራሽ ይሆናል ተብሎ ታስቦ የነበረው ሳይፍ ጋዳፊ መጋቢት 28/2003 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙኃን የተናገራቸው ናቸው፡፡

ከሶማሊያዊ ፍልሰተኛ ራህማ አቡካር አሊ ጋራ የተደረገ ቃለ-መጠይቅ። (ቪኦኤ /አብዱላዚዝ ኦስማን)

የቪድዮ እማኝነት፤ ሳማ ቱንካራ፤ ዕድሜ 23፤ ማሊ፡- ሳማ ቱንካራ ወደ ሰሜን ሊያርገው ያሰበውን የእግር ጉዞ ከመቀጠሉ በፊት በጣልያን ቀይ መስቀል ማኅበር በሚተዳደረው ጊዘያዊ መጠለያ ውስጥ ጥቂት ለማረፍ እየሞከረ ነው፡፡

በ2006 ዓ.ም የበልግ ወራት (በኢት. አቆ) ሥር እየሰደደ ከመጣው የማሊ ጦርነትና ሥራ ማጣቱንም ሸሽቶ የወጣው ረዥሙ የባማኮ ልጅ ወደ ጋኦ ሄደና ከዚያም የአልጀሪያን ድንበር አቋርጦ ታማንራሴት ገባ፡፡ ጋርዳይዳ ውስጥ ለስድስት ወራት ያህል ግንባታ ላይ ከሠራ በኋላ ወደ ሊብያ ሄደ፤ እዚያ ግን ሁኔታዎች ሁሉ የከፉና የባሱ ነበሩ፡፡

“ትሪፖሊ ውስጥ ሰዎች በየዕለቱ መሣሪያ እየያዙ ይመጡና ገንዘባችንን ይቀሙን ነበር፡፡ ወይም ደግሞ አንዲት የምትሠራ ሥራ አለች ብለው ይዘውን ይሄዱና ያለንን ሁሉ ይዘርፉናል” – ይላል ሳማ ቱንካራ ያሳለፈውን ሕይወቱን ሲያስታውስ፡፡

አንድ ምሽት ላይ የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች መጥተው ካምፓቸውን እንዲያፀዳላቸው ከጠየቁት በኋላ ሥራውን ሲጨርስ አፈሙዝ ደግነውበት አስፈራሩት፡፡ ምን አጥፍቶ? የሠራሁበትን ክፈሉኝ ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ከዚያ አጋጣሚ በኋላ ከሃገሩ ለመውጣት ወሰነ፡፡ ሜዲቴራኒያን ባህርን በ146 ፍልሰተኛ በታጨቀች ጀልባ ላይ ተሣፍሮ ሲያቋርጥ ‘አሁን እሞታለሁ’ ብሎ እያሰበ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በገላጣው ባሕር ላይ ካደረጉት የሰባት ሰዓታት ቀዘፋ በኋላ አንዲት የአውሮፓ መርከብ ደረሰችና አወጣቻቸው፡፡

ከማሊያዊ ፍልሰተኛ ሳማ ቱንካራ ጋራ የተደረገ ቃለ-መጠይቅ። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

የቪድዮ እማኝነት፤ ዳልማር እና አሕመድ፤ ዕድሜ 16 (የሁለቱም)፤ ኢትዮጵያ፡- ጣልያን ውስጥ ወደ አንድ ወር ያህል አካባቢ ቢቆዩም እነዚህ ታዳጊዎች አሁንም እውነተኛ ስማቸውን መናገር ይፈራሉ፡፡

ሁለቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ወደ አውሮፓ ጉዞ እንዲጀምሩ ያማለላቸው እዚያ ያሉ ጓደኞቻቸው የጀመሩት አዲስ ሕይወት ነበር፡፡

“ሃገራችንን ጥለን የወጣንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ – ይላል አሕመድ፤ – ሥራ አጥነት አለ፤ ከእኛ በፊት ትምህርት ቤት የጨረሱ ሥራ ፈት ሆነው በየመንገዱ ይንቀዋለላሉ፡፡ ስለዚህ ለመውጣት ወሰንን፡፡”

አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ አሸጋጋሪዎች ከሱዳን ድንበር የስምንት ሰዓት የእግር ጉዞ ሲቀር በመኪና አደረሷቸውና ሰሃራን ለማቋረጥ ከተዘጋጁ ሌሎች ፍልሰተኞች ጋር ተቀላቀሉ፡፡ በእግራቸውና እየለመኑ በሚወስዷቸው ፒክአፖች ለአምስት ቀናት ያህል ከተጓዙ በኋላ ከቤንጋዚ በስተደቡብ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው የሊብያይቱ አል ዋሃት ወረዳ ማዕከል አጅዳቢያ ደረሱ፡፡

በበረው ውስጥ ለአምስት ቀናት ከተጓዙ በኋላ ውኃ እንዳለቀባቸውና ይበልጥ አረመኔ ለሆኑ አስተላላፊዎች መሰጠታቸውን አሕመድ ይናገራል፡፡ እነዚያ ጨካኝ አስተላላፊዎች ፍልሰተኞቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው እየደወሉ ገንዘብ እንዲልኩላቸው እንዲነግሯቸው ሲያዝዟቸው ካልፈፀሙ ያለማቋረጥ በጭካኔ ያሰቃይዋቸዋል፡፡

ዴልማር በሊብያ አስተላላፊዎች መቀመቅ ውስጥ ለስድስት ወራት ያሳለፈውን መከራ ጠባሳዎቹ ይመሠክራሉ፡፡

ማንነታቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የ16 አመት ወጣት ፍልሰተኞች ከኢትዮጵያ ተነስተው ወደ ጣልያን ከተማ ሚላን ያደረሳቸውን ገሃነማዊ ጉዞ ሲያብራሩ። (ቪኦኤ /አብዱላዚዝ ኦስማን)

የቪድዮ እማኝነት፤ ሞሮ ሳኔ፤ ዕድሜ 16፤ ጋምቢያ፡- ሮም በምትገኝ አንዲት አነስተኛ የፍልሰተኞች መጠለያ ውስጥ ያለው ሞሮ ሳኔ ከቤቱ ሾልኮ የወጣባትን ሌሊት ያስታውሳል፡፡ የ2015 ዓ.ም (በአው. አቆ.) የአዲስ ዓመት ዋዜማ ነበር፡፡ በፕሬዚዳንት ያያ ጃሜ ላይ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ በመፍራት ሃሣቡን ለቤተሰቡ እንኳ ሳያካፍል ጠፋ፡፡ የሴኔጎሏ ከተማ ካኦላክ ደረሰና ወደ ማሊ ዋና ከተማ ባማኮ እንዲወስዱት ሦስት ሺህ ዶላር ከፈለ፡፡ እዚያም መንገድ ላይ ውኃ እየሸጠ ለአንድ ወር ያህል ቆየ፡፡ የኒዠሯ አጋዴዝ ውስጥ ጡብ ደርዳሪ ሆነ፡፡ ትሪፖሊ ውስጥ ኪሱ ውስጥ ቀርታው የነበረችውን ትንሽ ገንዘብ ፖሊስ ወሰደበትና ለ33 ቀናት አሠሩት፡፡

አሁን ሳኔ ስዊድን ለመግባት ቆርጧል፤ እንዲያም ሆኖ ግን “ያለፍኩበትን መንገድ እንደገና ሂድበት ቢሉኝ፤ አሁን አላደርገውም፡፡ በአደጋ የተሞላ ነው” ሲል የአውሮፓን ሕይወት ለማደን ከየቤታቸው የመነሣት ሃሣብ ያላቸውን አፍሪካዊያን ያስጠነቅቃል፡፡

ከጋምቢያዊ ፍልሰተኛ ሞሮ ሳኔህ ጋራ የተደረገ ቃለ-መጠይቅ። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

ክፍል አራት፡- አሸጋጋሪዎቹ

ክፍል አራት፡- አሸጋጋሪዎቹ አረመኔው “ማጋፌ”

አንድ ፍልሰተኛ አሸጋጋሪዎች ያደረሱበትን የአካል ጉዳት ያሳያል (በቪኦኤ የተገኘ / ኒኮላስ ፒኖ)

ፍልሰተኞችንና ስደተኞችን ማሸጋገር በየመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ያሳፍሳል፡፡ ደግሞም ዓለምአቀፍ ሕገወጥ የድብቅ ድርጅቶች ያንን ወረት በማግበስበስ በእጅጉ እየሰለጠኑበት ይሄዳሉ፡፡ የፍልሰተኞቹን የተሻለ ሕይወት ተስፋ እየተጠቀሙ መደበኛ ያልሆኑ ወይም ያልተለመዱ ወደ አውሮፓ ሊያደርሱ የሚችሉ መንገዶችን ማሳየት የሚጠቀሙበት ቁልፍ አሠራራቸውና የበዛው ብዝበዛቸውም መሣሪያ ነው፡፡

ከኻርቱም እስከ ካላዪ ያለው የሥቃይና የእንግልት ታሪክ በሚታክት ሁኔታ ተመሣሣይ ነው፡፡ አሸጋጋሪዎቹ በበረሃው ውስጥ ፍልሰተኞቹን ማሰቃየታቸው፤ የተጤሰ ሲጋራ እጆቻቸው ላይ፣ ፊቶቻቸው ላይ፣ ደረቶቻቸው ላይ ማጥፋታቸው፤ እጅግ በተጨናነቁትና የበረሃውን አሸዋ በሚቀዝፉት የጭነት መኪኖች ላይ የሰው ልጅን እንደዕቃ ቀርቅበው እያሰሩ መጫናቸው፤ ሊብያ ሲደርሱ ማስለቀቂያ ለማስከፈል እሥር ቤቶች ውስጥ ማጎራቸው፤ ታሪኩ ተመሣሣይና የአዙሪት ነው፡፡

ማንነቱ እንዲገለፅ ያልፈለገ ኤርትራዊ ፍልሰተኛ ሰለ ፈታኙ የሊቢያ ጉዞ ይናገራል። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

“አንዳንዴ ማጋፌዎቹ ምግብ የምናበስልበት እንጨት ወይም ከሰል ላይሰጠን ይችላል፡፡ ምግብ የሚያበስሉልን ሰዎች በረሃብ እንዳንሞት ያንዳንዶቻችንን ጫማ ወይም ጃኬት እያነደዱ ይቀቅሉ ነበር፡፡”

– ሃፍሳ፤ ሶማሊያዊት በሮም፡፡ “ማጋፌ” አስተላላፊዎቹን ለመጥራት የሚጠቀሙበት የሶማሊኛ ቃል ነው፡፡ ትርጉሙ “አይምሬ” እንደማለት ነው፡፡

ከሱዳናዊ ፍለሰተኛ አብደላህ አርኩ ጋራ የተደረገ ቃለ-መጠይቅ። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

ጣልያን ውስጥ እንኳ አሸጋጋሪዎቹ የሚንቀሣቀሱትና የሚሠሩት በግላጭ ነው፡፡ አንድ ኤርትራዊ ለቪኦኤ በሰጠው ቃል እንዳይመዘገብ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ተናግሯል፡፡ ሌሎች ደግሞ በመቶዎች ሺሆች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለማስለቀቂያ ክፍያ እስኪያሰባስቡ ካታንያ ውስጥ በአንድ ቤት ለአሥር ቀናት ያህል ተይዘው ቆይተዋል፡፡

የጣልያን ከተማ ሚላን ውስጥ በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ተይዞ የቆየ ማንነቱ እንዲገለፅ ያልፈለገ የ16 ዓመት ኢትዮጵያዊ ወጣት። (ቪኦኤ /አብዱላዚዝ ኦስማን)

ጉዟቸውን ለመቀጠል አቅም ያላቸው ሕገወጥ የሆኑ መንገድ መሪዎችን መረብ መጋፈጥ ይኖርባቸዋል፤ እነዚያ መንገድ መሪዎች ደግሞ እንደየአካባቢው መልክአምድራዊ ሁኔታ የሚለዋወጡ ናቸው፤ ሜዲቴራኒያንን ከሚያሻግሩ የፍልሰተኛው ሃገሬ ሰዎች ሰሜናዊ ፈረንሣይ ውስጥ መጠለያ ሠፈሮችን እስከሚያዘጋጁ የአልባኒያ ማፊያ ቡድኖች አባላት፡፡ በርግጥ ገንዘብ ጨርሶ የሌላቸውም ቢሆኑ ጉዟቸውን ወደ ሰሜን መቀጠል ይችላሉ፤ ብርቱ ውል ግን መፈረም ይገባቸዋል፡፡ ዕዳቸውን በሥራ ሊከፍሉ፡፡ የዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት – አይኦኤም ባልደረባው ጆቫኒ አባቴ እንደሚለው ወጣቶቹን ሴቶች የሚጠብቃቸው ተገድደው ሴተኛ አዳሪነት መግባት ነው፤ የሚያገኙት ገንዘብ ወደ አሻጋሪዎቻቸው የሚገባ ይሆናል፡

ጠበቃና የIOM ወይም የአለም አቀፍ የፍለሰተኞች ድርጅት ሃላፊ ጂዮቫኒ አባቴ ጋራ የተደረገ ቃለ-መጠይቅ። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

ክፍል አምስት፡- ማጠቃለያ

ክፍል አምስት፡- ማጠቃለያ ከፊት ያለው መንገድ፤ የተንጠላጠሉ ሕይወቶችና በቋፍ ያለው ፖሊሲ

“The Jungle” ወይንም “ጫካው” ብዙ ሺህ ፍልሰተኞች ከፈረንሳይ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በሕገ-ወጥ መንገድ አቋርጠው ለመግባት እስኪሞክሩ ድረስ የሚኖሩበት መንደር ነው። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

ድኅነት የደቆሣትን ሶማሊያዊቱን የሁለት ልጆች እናት ኒምኮ ሙሴ አሕመድን ከሶማሊያ ያሳደዳት የአል-ሸባብ አማፂያን በሃገሪቱ ውስጥ የፈጠሩት የሚበርድ የማይመስል ጥፋትና ፍርሃት ናቸው፡፡ በዓለም የመጨረሻውን ግዙፍ በርሃ ሰሃራን፤ እንዲሁም አንድ የጦርነት ቀጣናና ባሕሩን በአንዲት ላንቁሶ ጀልባ  አቋርጣ ወደ አውሮፓ ልታመራ ተነሣች፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሃብት ሠንጠረዥ ላይ ቁንጮውን ቦታ እየያዘች የምትገኘው የኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪየና የምትታወቀው “የምኞቶች ከተማ” በሚል የቁልምጫ መጠሪያ ነበር።

ኒምኮ ኑሮ ሲጨልምባት ቀድሞ የወታደር መኖሪያ በነበረ ግቢ ውስጥ ካለ ሕንፃ ጣሪያ ላይ እራሷን ቁልቁል የሲሚንቶው ወለል ላይ ወረወረች፡፡

በመንግሥት በሚደገፈው ትራይኪርቼን የስደተኞች መጠለያ ሠፈር ውስጥ ሆና ዛሬ ታሪኳን የምትናገረው ሚንኮ “ለበርካታ ቀናት ነፍሴን ስቼ ሳጣጥር ነበር የቆየሁት። ከዚያ ሁለት እግሮቼና የአከርካሪ አጥንቴ ተሰብሮ ሕይወቴ ተረፈች” ትላለች፡፡

እራሷን ለማጥፋት የመሞከሯ ምክንያቱ ለጥገኝነት ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ነበር። ከቀዬዋ ያሳደዳት ፍራቻ፣ አሁን ተስፋ በመቁረጥ ተተክቷል።

“አፍሪካዊያን በተለይ ሶማሊያዊያን እኔ የምመክራችሁ ‘አውሮፓ ምንም የለም፤ ከህልማችሁ አውጡት” አለች ሚንኮ።

“ዕውነቱን አሁን እያየሁት ነው፡፡ በረዶውን፡፡ እዚህ እየራበኝ እንዳለ፤ አፍሪካ ውስጥ ርቦኝ አያውቅም፡፡”

– ኒምኮ ሙሴ አህመድ፤ ኦስትሪያ ያለ ሶማሊያዊ ስደተኛ፡፡

ከሶማልያዊ ፍልሰተኛ ኒምኮ ሙሴ አህመድ ጋራ የተደረገ ቃለ-መጠይቅ። (ቪኦኤ /አብዱላዚዝ ኦስማን)

እንደ ሚንኮ ያሉ ታሪኮች ብዙ ናቸው፤ ከሰሃራ በስተደቡብ ካሉ የአፍሪካ ሀገሮች የሚሰደዱ ሰዎች በዚህ መሰል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያልፋሉ።

ሚንኮ ባለፈው ዓመት ብቻ አውሮፓ እንደገቡት አንድ ሚሊዮን ስደተኞች ሁሉ ቤተሰቦቿን ጥላ፤ ጥሪታቸውን በበረሃና በባሕር ላይ ከሞት ጋር ለመቆመር ስትል አንጠፍጥፋ አውጥታ አሁን ባይተዋር በሆነችበት ሰሜናዊ አህጉር ውስጥ መጠለያ የለሽ የመንገድ ላይ ሰው፤ ፓስፖርትና ሃገር የሌላት ለመሆን ተዳርጋለች፡፡

አንዳንዶቹ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው፣ ሌሎች ሀገራቸው ውስጥ እየጣሏቸው ተሰድደዋል። መንገዱ አስቸጋሪ ነው። በባህር ላይ ሰጥመው የሚሞቱ ቁጥር እንዲህ በቀላል የሚቆጠር አይደለም፡፡

ከሞትና ከመከራ ተርፈው አውሮፓ ከደረሱ በኋላም ፈተናቸው ብዙ ነው። ሚንኮ እንደምትለው፣ በስደተኞቹ መካከል እራሱ የማግለልና የንቀት ስሜት አለ፡፡

ተንቀሳቃሽ ስልክ ጠፋ ተብሎ በሶርያውያን ስደተኞችና በአፍሪካዊያኑ መካከል የተፈጠረው ግብ ግብ እጅግ አድርጎ አስቀይሟታል።

የተሻለ ትምህርት ያላቸው አፍጋናዊያን ስደተኞች የራሣቸውን ታሪክ ለመጠለያ ሠፈሩ ባለሥልጣናት በተሻለ ሁኔታ መግለፅ ስለሚችሉ ስልኩን ከአፍሪካ የሄዱት ወሰዱትም አልወሰዱት ጥፋተኞች ይሆናሉ፡፡

አፍሪካውያን ፍልሰተኞች የሚያርፉባቸው ዋና ዋና የአውሮፓ መድረሻዎች

የአውሮፓ ኮሚሽንን ምንጭ አድርጎ የተቀናበረው ካርታ አብዛኛ ከሰሀራ በስተደቡብ ካሉ ሀገሮች የሚነሱ ፍልሰተኞች በጣልያን አልፈው የሚያርፉባቸው ዋና ዋና የአውሮፓ መድረሻ ከተማዎችን ያሳያል።

በቋፍ ያለ ፖሊሲ

እንደ አሕመድ ላሉ ስደተኞች ቀላል የሚባሉ መልሶች የሉም፡፡ በ2007-2008 ዓ.ም (በኢት.አቆ.) ታይቶ በማይታወቅ ቁጥር በፈሰሰ የስደት ጎርፍ ውስጥ በሚገኘው፤ በግሪክ የዕዳ ውዝግብ ውስጥ በከረመው፤ በበርካታ የሽብር ጥቃቶች በተመታው ባለ ሃያ ስምንት አባል ሃገሩ በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ለችግሮች መፍትኄ ለማግኘት ያስችላል የሚባል የአንድነት ሃሣብ ብዙም ያለ አይመስልም፡፡

በቅርቡ የወጣው የአውሮፓ ኅብረት የምጣኔ ኃብት ትንበያ በያዝነው ዓመት ውስጥ ሦስት ሚሊየን ተጨማሪ ፍልሰተኞች ወደአውሮፓ ሊገቡ እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም የአውሮፓ ሠልስቱ ሃያላን ተብለው ከሚጠሩት ሃገሮች አንዷ የሆነችው እንግሊዝ ከኅብረቱ ትውጣ ወይስ ትቆይ በሚል ሃሣብ ላይ ውሣኔ ሕዝብ ለመጥራት መወሰኗ ኅብረቱን ወደ መሰነጣጠቅ ሊወስደው ይችላል የሚል ሥጋት አጭሯል፡፡

ከ“The Jungle” ወይንም “ጫካው” አጠገብ የሚገኘው የCalais (ካሌ) ወደብ አጥር። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

ከ“The Jungle” ወይንም “ጫካው” አጠገብ የሚገኘው የCalais (ካሌ) ወደብ አጥር። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

ቀውሱን ሊያስወግድ ይችላል የሚል ተዓምራዊ መፍትኄ የአውሮፓ ኅብረት ፖሊሲ አውጭዎች የላቸውም፡፡ ምንም እንኳ 160 ሺህ ተቀባይነት ያገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በአባል ሃገሮች ውስጥ ለማስፈር ቃል ተገብቶ የነበረ ቢሆንም እስከ ታኅሣስ 2/2008 ዓ.ም (በኢት.አቆ.) በነበረው ጊዜ የሠፈሩት 159 ብቻ ነበሩ፡፡ ታኅሣስ 1/20228 (በኢት.አቆ.) ካናዳ የመጀመሪያዎቹን 25 ሺህ የሦሪያ ስደተኞችን ያሣፈሩ አይሮፕላኖችን በፀጋ አስተናግዳለች፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ግን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ያቀረቡትን አሥር ሺህ የሦሪያ ስደተኞችን የመቀበልን ሃሣብ የሃገሪቱ እንደራሴዎች እንደገና ሊመክሩበትና ሊከራከሩበት ተነጋግረዋል፡፡ ተጋግሎ እየተካሄደ ባለው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ ውስጥ የኢሚግሬሽን ጉዳይ ፅንፍና ፅንፍ የሚያስይዝ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩዎች ዘመቻ እየመሩ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ማንኛውም ሙስሊም ወደ አሜሪካ እንዳይገባ እንዲታገድ እና ከተመረጡም በኦባማ መርኃግብር የገቡ ሦሪያዊያንን ሁሉ መልሰው እንደሚያስወጡ ዝተዋል፡፡ በኢሚግሬሽን ፖሊሲ ላይ የኦባማ አስተዳደር የጎላ እንቅስቃሴ ቢያደርግም ለቀድሞ አፍጋናዊያንና ኢራቃዊያን የጦር ሜዳ አስተርጓሚዎች ቪዛ እንዲሰጥ እየተደረገ ያለው ጥረት እንኳ በሚያሣዝን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

“The Jungle” ወይንም “ጫካው” የፍልሰተኞች መንደር በCalais/ካሌ-ፈረንሳይ። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

“The Jungle” ወይንም “ጫካው” የፍልሰተኞች መንደር በCalais/ካሌ-ፈረንሳይ። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

የአውሮፓ ሃገሮች በተናጠል የጥገኝነት ጥያቄ ማመልከቻዎችን ሲሆን ጣልያንና ግሪክ ውስጥ ባሉ የስደተኞች መጉረፊያ ጣቢያዎች ውስጥ ሥራው በአብዛኛው በዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች፣ በበጎ ፍቃደኞችና በማዘጋጃ ቤቶች ባለሥልጣናት የይድረስ ይድረስ ሩጫ እንዲከናወን ተገድዷል፡፡

“እዚህ ቀውስ ውስጥ ከገባን ወራት ካለፉ በኋላም ለምን ይሆን ወደ አውሮፓ የባሕር ዳርቻዎች ለሚደርሱት ሰዎች ብዙው የነፍስ አድን እርዳታ ሥራ በአብዛኛው በበጎ ፍቃደኞች ብቻ እንዲከናወን የተደረገው?” ሲሉ ይጠይቃሉ የሂዩማን ራይትስ ዋች የአጣዳፊ ሁኔታዎች ዳይሬክተር ፒተር ኤን ቦካር በቅርቡ ግሪክ ውስጥ ከተፈጠረው የስደተኞች ብዛት ጭንቅንቅ በኋላ ሲፅፉ – “ለምን ይሆን አንድም መንግሥት ወይም ሕብረ-መንግሥታዊ ድርጅት አምቡላንስ እንኳ ሲያቀርብ በማይታይበት ወይም ሃሣቡ እንኳ በሌለበት ሁኔታ እስከዛሬ በሌዝቦስ ቋጥኞች ላይ የነፍስ አድኑን የሕክምና ሥራ በጎ ፍቃደኞች የሚያከናውኑት?”

በቀውሱ ግንባር ላይ የአውሮፓ ኅብረትን ተጠሪዎች ማግኘት እጅግ ከባድ መሆኑን እየጠቆሙ ይህንን ወቀሣ አንዳንድ የዜና ዘገባዎችም አስተጋብተውታል፡፡

“የድንበር ጥበቃና አስተዳደር ጉዳይ በቅድሚያ የየሃገሩ ባለሥልጣናት ኃላፊነት ነው” ብለዋል የአውሮፓ ኮሚሺን ቃል አቀባይ በኢሜል በሰጡን ቃል፡፡ “የአውሮፓ ኮሚሺን እና የአውሮፓ ኅብረት ተቋማት አባል መንግሥታትና የየሃገሩን ባለሥልጣናት በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በመያዝና በመምራት ሥራዎች ላይ እገዛ ያደርጉላቸዋል፡፡ አባል መንግሥታትን መተካት ግን አይችሉም፡፡

ከ“The Jungle” ወይንም “ጫካው” አጠገብ የሚገኘው የCalais (ካሌ) ወደብን የሚጠብቁት ፖሊሶች። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

ከ“The Jungle” ወይንም “ጫካው” አጠገብ የሚገኘው የCalais (ካሌ) ወደብን የሚጠብቁት ፖሊሶች። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

ከሃገር ውስጡ ፖሊሲ በተጨማሪ የአውሮፓ ኅብረት ከአፍሪካ የሚነሱትን ስደቶች ሥር-ወሰበብ ለመጋፈጥ እየፈለገ ነው፡፡ ኅዳር ውስጥ በፍልሰት ላይ በተካሄደ ጉባዔ ላይ የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች የአፍሪካ ሃገሮች ከስደት የሚመለሱ ወይም የተፈናቀሉ ዜጎቻቸውን መቀበልና መልሰው ማቋቋም እንዲችሉ የሚረዳቸው የ1.9 ቢሊዮን ዶላር አጣዳፊ የመተማመኛ ጥሪት ወይም ትረስት ፈንድ አቋቁመዋል፡፡ የሜዲቴራኒያኗ ደሴት መንግሥትና በአንድ ወቅት ዋነኛዋ የፍልሰት መድረሻ የነበረችው ይህንኑ የመሪዎች ጉባዔ ያስተናገደችው ማልታ 270 ሺህ ዶላር ለመለገስ ቃል ገብታለች፡፡

ከአንድ ወር በኋላ የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት ዋና ዋና የስደት ምንጭ በሆኑ ሃገሮች ወስጥ ሥራ ፈጠራን በማፋጠንና የልማት መርኃግብሮችን በመዘርጋት ከአፍሪካ የሚነሳውን ፍልሰት ለመቆጣጠር ያስችላል ያሉትን የሁለት ቢሊዮን ዕቅድ ይፋ አደረጉ፡፡

የሜዲቴራኒያንን ተፋሰስ ከጋዳፊ መውደቅ በፊት ወደነበረው መረጋጋት ለመመለስ ግዙፍ የሆኑ ሥልቶች መቀረፅ ይኖርባቸዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም (በኢት.አቆ.) ያኔ የጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ፍራንኮ ፍራቲኒ አዲስ ዓይነት አህጉር ዘለል አካባቢያዊ ሥርዓት እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

“ወደ ፈረንይና ወደ ጣልያን ለማቋረጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጥቁሮች ወደ ሜዲቴራኒያን ይመጣሉ፡፡ በሜዲቴራኒያን ፀጥታ ጉዳይ ላይ ሊብያ ሚና ይኖራታል፡፡”

– ሞአማር ጋዳፊ ለፍራንስ 24 ቴሌቪዥን በመጋቢት 2003 ዓ.ም ከሰጡት ቃል የተወሰደ፡፡

“የአውሮፓ ኅብረት፣ ሌሎቹ የዓለም ኃያላን ሃገሮችና የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉን የገንዘብ ድርጅትን የመሣሰሉ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ለሜዲቴራኒያን የምጣኔ ኃብት መረጋጋት የሚሠራ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሜሪካ ለምዕራብ አውሮፓ ሃገሮች ማገገሚያና መልሶ ግንባታ ዘርግታው እንደነበረው ዓይነት መርኃግብር ወይም ማርሻል ፕላን ሊያወጡ ይገባል” ብለው ነበር ፍራቲኒ በአውሮፓ አቆጣጠር በ2011 ዓ.ም ፋይናንሻል ታይምስ አስተያየት ማስፈሪያ ገፅ ለይ አውጥተውት በነበረ ፅሁፋቸው፡፡ “ይህ ዕቅድ ግዙፍና እጅግ አስፈላጊ የሆኑ አዲስ የአውሮፓና ዓለምአቀፍ የገንዘብ ምንጮችን በአካባቢው የየሃገሮቹን ምጣኔ ኃብት ለማሳለጥ እና የመዋዕለ ነዋይ ፍሰትን ለማብዛት የሚያስችል በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ ማንቀሳቀስ መቻል አለበት፡፡”

በሜዲቴራኒያን ሃገሮች መካከል ያሉ የንግድ መሰናክሎችን የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት ማንሣት እንዳለባቸውና “እጅግ ቁልፍ ሥፍራ ያላት” ካሏት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋርም በስትራተጂው ላይ መመካከርና አብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ ፍራቲኒ መክረዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ዕድሎች እንዲጠናከሩና ወጣቶች በሽብር ድርጅቶች እንዳይማለሉ ለማድረግም የሥራ ኃይሉን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ “ሜዲቴራኒያን ዘለል የሥራ ሥልጠና መርኃግብሮችን መዘርጋት ሕገወጡን ፍልሰትና አስተላላፊነት ለማስቆም የሚያስችል እጅግ የተመረጠው መንገድ ነው” ብለው ነበር፡፡

በተመሣሣይ ሁኔታ ደግሞ ችግሩን የሚፈልሱ ሰዎችን ከአፍሪካ የሚገፉ ጉዳዮችን በመጋፈጥ ብቻ መፍታት እንደማይቻል አንድ ታዋቂ የፍልሰት ጉዳዮች ተንታኝ ተናግረው ነበር፡፡

“አውሮፓ ውስጥ ያለው እውነተኛው ቀውስ የጋራ ወደሆነ ምላሽ ለመምጣት አለመቻል ነው” ብለዋል የአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጥናት ምሁሩ ሃይን ደ ሃስ ለሃፊንግተን ፖስት ጋዜጣ ሲናገሩ፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ስምምነቶች ጥበቃ ከሚደረግላቸው ከግጭቶች አካባቢዎች ከሚሸሹ ስደተኞችና በፖለቲካ ወከባ ምክንያት ከሚሳደዱ ጋር የተዳመረው የአውሮፓ የምጣኔኃብት ክፍትነት እያደገ መምጣት ከሚፈጥረው ርካሽ የፍልሰተኛ ጉልበት ጋር ገዳቢ የሆኑት የኢሚግሬሽን እርምጃዎች አይጣጣሙም፡፡

“ለሃያ አምስት ዓመታት የዘለቀው የአውሮፓ እራሷን አጥራና ከልላ መኖር ሙሉ በሙሉ የፎረሸ አካሄድ ነው” ብለዋል ሃይን ደ ሃስ፡፡ “ሰዎች በዚህም በዚያም መግባታቸው አልቀረም፤ የተፈጠረው ብቸኛ ነገር ቢኖር ምንድነው፤ ሕገወጡ ማሸጋገር፣ የፍልሰተኞች ሥቃይና እንግልት፣ ድንበር ላይ የሚጠፋው ሕይወት በረከተ፡፡”

በፍልሰተኞች የተጣሉ ድንኳኖች-”ጫካው” (The Jungle)- Calais/ካሌ-ፈረንሳይ። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

በፍልሰተኞች የተጣሉ ድንኳኖች-”ጫካው” (The Jungle)- Calais/ካሌ-ፈረንሳይ። (ቪኦኤ/ ኒኮላ ፒኖ)

ግዙፎቹ የልማት ስትራተጂዎች ትውልድ አቋራጭ ጊዜን ስለሚጠይቁና በተጨማሪም በመፍለስ በሚፈልገው ሰው ፍላጎትና በአውሮፓ ኅብረት የንግድና የኢሚግሬሽን ፖሊሲ መካከል መጣጣም ስለሌለ – የሚሉት ብራስልስ የማገኘው የፍልሰት ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ኤልሳቤጥ ኮሌት – የሚሻለው አነስ ያሉና አካባቢያዊ በሆኑ የምጣኔ ኃብት ዕቅዶች ላይ መሥራት እንደሆነ ይመክራሉ፡፡

ምናልባት የአውሮፓ ኅብረት የጋዳፊዪቱ ሊብያ ትሰጥ የነበረውን ሁሉ መልሶ ማምጣት የሚያስችል ጥረት ማድረግ ላይ ማትኮር ይኖርበት ይሆን እንዴ? የሚል ጥያቄም እየተነሣ ነው፡፡ እንደ ኒምኮ ሙሴ አሕመድ ላሉ ሰዎች ቀድሞ ወደሚያውቁትና ሸሽተውት ወደወጡት ሕይወት የማይመልሳቸው፣ ከአውሮፓ አዲስ ሕይወት ጋርም ትንቅንቅ ውስጥ እንዲገቡ የማያደርጋቸው ዕቅድ አነስ ያሉ ዕዳገትና ሥራን የሚያበዙ የኢንዱስትሪ መናኸሪያዎችን መፍጠር ይሻል ይሆን?

ወደኋላ መመለስ የለም

አጫጭር የማረጋጊያ ዕቅዶችም ቢሆኑ ከጋዳፊ በኋላ እንደተፈጠረችው እጅግ ለተናጠችውና መሹለኪያ ብዙ በመሆኗ በአውሮፓ ኅብረት ሃገሮች ውስጥ ሁሉ ፍልሰተኛ-ጠል አስተሳሰብ እንዲፈጠር ምክንያት ለሆነችው ሊብያ መሰል ሃገር የመሥራታቸው ነገር ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ በፍልሰት ጉዳይ ላይ ፖሊሲ አውጭዎች መፍትኄ ናቸው የሚሏቸውን መላዎች እያበጣጥሩ ባሉበትም ሁኔታ ቢሆን መልስ የሚገኘው ብራስልስ ካሉ ፌደራል ቢሮዎች ሳይሆን መፈናቀል ታሪኮች በሚጀመሩባቸው ሥፍራዎች ነው፤ የአደጋውን መዘዝና በኋላ ይገኛል ተብሎ የሚታለመውን ግብ በአግባቡ ባለማመዛዘን ወይም ብዙ ጊዜ ደግሞ ግድየለሽነት በበዛበት ሁኔታ በሚወሰዱ እርምጃዎች በመከራ የተዋጡ መንገዶች በሚጀመሩባቸው ሥፍራዎች፡፡

ፒተር ኮበስ ለዚህ የሪፖርቱ ክፍል ከዋሽንግተን ዲሲ ዘግቧል።

መሰናዶ

ዘገባ፡- አብዱላዚዝ ኦስማንና ኒኮላ ፒኖ

ኤዲተር፡- ፒተር ኮበስ

የድረገጽ ቀረጻና መሰናዶ፡- Stephen Mekosh and Dino Beslagic.

የስራ አስተባባሪ፡- ስቲቨን ፌሪ.

ዝግጅት፡- ተፈራ ግርማና እዝራ ፍሰሃዬ

ትርጉም፡- የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት

አስተያየቶች